
(ይህንን ጽሁፍ አብዛኛውን በቀጥታ በመተርጎም የተወሰነውን ደግሞ አቻ ትርጉም በመፈለግ Inspire Business Solution.com ከተሰኘ ድረ ገጽ ላይ የወሰድኩት ነው)
"ብዙ ሰዎች ኢሞሽናል ማቹሪቲን ከኢሞሽናል ኢንተሊጀንስ ጋር በማቀላቀል ወይም በመቀያየር ሲጠቀሙበት በብዛት ይስተዋላል። ይህ ግራ መጋባት በምሁራንም ሆነ በተቋማት ደረጃም ሲምታታ ይታያል።" በማለት ይገልጸዋል ፒተር ቫጅዳ (ዶ/ር) የተባለ በሙያወ ተመራማሪ በ2013 እኤአ ባሳተመው "True North Partnering" በተባለ ጽሁፉ ላይ። በተጨማሪም ሲያብራራ ፣ "የሁለቱ ጽንሰ ሐሳቦች መቀላቀል በአጠቃላይ በአለማችን ላይ በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚስተዋል ስለሆነ ብዙ መደነቅ አይገባም!" ይለናል። የዶክተሩን ማብራሪያ እንደመነሻ በመጠቀም ሰዎች የሁለቱን ጽንሰ ሃሳቦች መሰረታዊ አንድነት እና ልዩነታቸውን በመረዳት በተገቢው መንገድ መጠቀም ተገቢ እና አስፈላጊም ስለሆነ እንደሚከተለው ለማስረዳት እሞክራለሁ። የሚቀጥሉት ማብራሪያዎች ችግሩን ያስወግዳሉ ብዬም አስባለሁ።
ኢሞሽናል ኢንተሊጀንስ፡ ማለት "የራስን እና የሌሎችን ስሜት መረዳት ማለት ነው።" በማለት ዶ/ር ቫጅዳ ይገልጸዋል። በቅደም ተከተል ማስቀመጥ ካለብን ደግሞ የራስን ስሜት መረዳት ሲቀድም የሌሎችን ስሜት መረዳት ደሞ ይከተላል። በተለይም ከሰዎች ጋር በሚኖረን መስተጋብር ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ ስሜቶችን መረዳት ወሳኝ ነው። በተለይም የውይይቱን፣ ወይም የመነጋገሪያ አጀንዳውን በተሳካ ሁኔታ ለማስተላለፍ ወይም ክርክር ከሆነ የተከራካሪውን ክፍል ለማሳመንና ለመርታት መጀመሪያ የራሳችንን የስሜት ተክልቁመና ምን ይመስላል ብለን መረዳት ወሳኝ የመጀመሪያ እርምጃ ነው።
በመቀጠልም ዶ/ር ቫጅዳ ሲያብራራ፣ ተከራካሪያችን ወይም ተፎካካሪያችን በምን አይነት ስሜት ውስጥ ነው የሚገኘው ብለን መረዳት ይኖርብናል ይላል። ይህ ደሞ በቀጣይ በወይይላችን ውስጥ የምንጠቀማቸውን ቃላት፣ የምናነሳቸውን አጀንዳዎች እንዲሁም የምናሳያቸውን የሰውነት እንቅስቃሴዎች መጥነን እና አስልተን እንድናቀርብ ያግዘናል። እንደ ዶ/ሩ ማብራሪያ፣ ኢሞሽናል ኢንተሊጀንስ የተፎካካሪያችንን ስሜት ብቻ ሳይሆን የአድማጮቻችንንም ስሜት መረዳትን ይጠይቃል። አድማጭ ወይም ተመልካቹ በሚኖረን መስተጋብር ውስጥ እያሳየ(ን) ያለውን የስሜት ባህርይ መረዳት ተጨማሪ ድጋፍ ለማግኘት ተፎካካሪንም ለማሳመን ወሳኝ ምዕራፍ ነው።
ኢሞሽናል ኢንተሊጀንስ ለኢሞሽናል ማቹሪቲ መንደርደሪያ ነው። አንድ ግለሰብ ኢሞሽናል ኢንተሊጀንስ ሳያዳብር ወይም ሳይኖረው የኢሞሽናል ማቹሪቲ ላይ መድረስ ወይም መብቃት አይቻለውም።
"ኢሞሽናል ማቹሪቲ ማለት ያዳበርነውን የኢሞሽናል ኢንተሊጀንስ እውቀት እንዴት ለሚፈለገው ጥቅም ማዋል እንዳለብን የሚያግዘን የብቃት ደረጃ ነው።" ይለናል ዶ/ር ፒተር ቫጅዳ። "ለምሳሌ!" ይላል ዶክተሩ።
"ለምሳሌ አንድ ኢሞሽናል ኢንተሊጀንስ አለው ብለን የምናስበው ሰው በክርክር ወቅት የራሱን የስሜት አይነት እና ደረጃ እንዲሁም የተከራካሪውን ወገን ስሜት ደረጃ እና አይነት መረዳት ችሏን እንብል። ከዛስ? መረዳት መቻሉ ስለ ተፎካካሪውም ሆነ ስለራሱ የስሜት ሁኔታ እና አይነት እውቀት አለው ማለት ብቻ ነውና። ይህ ግለሰብ በኢሞሽናል ኢንተሊጀንስ ብቃቱ ያካበተውን እውቀት እንዴት መጠቀምና የተፎካካሪውን/የተቃራኒውን አካል ማሸነፍ/ማሳመን እንዳለበት ካላወቀ የኢሞሽናል ማቹሪቲ የለውም ማለት ነው። ኢሞትናል ማቹቲቱ በራሳችን ስሜት አይነት እና ሁኔታ እንዲሁም ከእኛ ወጪ ባሉ አካላት ላይ ያለውን የስሜት አይነት እና ደረጃ እውቀት እንዴት ለምንፈልገው አላማ በምንፈልገው መንገድ መጠቀም እንዳለብን የሚረዳን "የብቃት ደረጃ ነው" ማለት እንችላለን" በማለት ያብራራዋል። ይህንን ፍልስፍና ባጭሩ እንደሚከተለው እንግለጸው።
ባጭሩ የኢሞችናል ኢንተሊጀንስ እና የኢሞሽናል ማቹሪቲ ግንኙነት ሲገለጽ የእውቀት እና የጥበብ አይነት ግንኙነት ማለት ነው። አንድ ሰው ያለ እውቀት ጥበበኛ መሆን አይችልም። ይህ ማለት ጥበበኛ ለመሆን መጀመሪያ ማወቅ አለብህ ማለት ነው። በማታውቀው ጉዳይ ላይ ጥበበኛ መሆን አትችልም እያልኩህ ነው። አንድ ሰው ምንም እውቀት በሌለው ጉዳይ ላይ በጥበብ እሰራዋለሁ ቢል ማህበረሰባችን "ወፈፌ!" ከሚለው የግለሰቦች ባህርይ አንዱ ነው ማለት ነው።
አንድ ምሳሌ ልጨምር።
የተቀበረ ፈንጂ ለማምከን መጀመሪያ ስለፈንጂ እውቀት ሊኖርህ ይገባል። አይነቱን፣ ባህርዩን፣ የጉዳት መጠኑን፣ እንዴት ማምከን እንደሚቻል፣ እንዴት ማፈንዳት እንደሚቻል ... ወዘተ። ከላይ የጠቀስኳቸው አንዳቸውም እውቀት የሌለው አንድ ሰው "በጥበብ" ፈንጂውን አመክናለሁ ቢል ወፈፌነት ደረጃ ላይ ነው ማለት ነው። ምክንያቱም ወደ ፈንጂው አካባቢ ለመጠጋት እንኳን እውቀት ሳይኖረው ጥበብ አለኝ የሚለው ወፈፌነቱ ጥበብ መስሎት ነው። ይህ አይነቱ ሰው እንደ እድል ሆኖ ፈንጂው ሳይፈነዳ መቆጣጠር ቢችል እንኳን እድል ከወፈፌነቱ ጋር ነበር ማለት ነው እንጂ ጥበበኛ ልንለው አይገባም።
የኢሞሽናል ኢንተሊጀንስ 5 መሰረታዊ መገለጫዎች
የሳይንስ ምርምር ጆርናሊስት የሆነው እና በዚሁ የምርምር ማእቀፍ ውስጥ በርካታ የምርምር ጽሁፎችን ያሳተው ዳነኤል ጎልድማን ኢሞሽናል ኢንተሊጀንስን በአምስት መሰረታው መገለጫዎች በተለይም "Working with Emotional Inteligence" በሚለው የቅርብ ጊዜ ሥራው ላይ ሊያስረዳ ሞክሯል። ይህየጎልድማን ጽሁፍ በሰኔ 28፣ 1999 እኤአ የታተመ ነው። በዝርዝር እንመልከታቸው።
1. ራስን ማወቅ፡ እንደ ጎልድማን አገላለጽ ከኢሞሽናል ኢንተሊጀንስ መገለጫዎች መሃል የመጀመሪያው እና መሰረታዊው ክፍል ነው። ጎልድማን እንዲህ እያለ ያብራራል፣ "የራሳችንን ወቅታዊ ሁኔታ እና ተነሳሽነት መረዳት፣ ለይቶ ማወቅ እና መረዳት እንዲሁም ሌሎች ላይ ሊፈጥር የሚችለውን ተጽዕኖ የመረዳት ችሎታ ነው።" ይህንን ቀለል ባለ መንገድ ሲገልጸ ደሞ፣ "ምን አይነት ሙድ ወይም ስሜት ውስጥ ነው ያለሁት? ደብቶኛል? እየተናደድኩ ነው? ወደ ጸብ ልገባ ነው? ... የሚሉት ለእራስ የሚጠየቁ ጥያቄዎች ያለንበትን ወቅታዊ የስሜት ሁኔታ ወይም አይነት ለመረዳት ይረዱናል" ይላል። ያለንበትን ወቅታዊ የስሜት ሁኔታ ከተረዳን በኋላ በራሳችንም ሆነ በሌሎች ላይ ምን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ መገንዘብ ይኖርብናል። በዚህ ወቅት ኢሞሽናል ማቹሪቲ ላይ የደረሰ ሰው የሚከተሉት መገለጫዎች ይኖሩታል።
- በራስ መተማመን፡
- በራሱም ሆነ በዙሪያው ባሉ ነገሮች ላይ ሙሉ የበላይነት እንዳለው ይረዳል
- በዙሪያው ያሉ ሰዎች/ታዳሚዎች/ ስለእርሱ ምን እንደሚረዱ እውቀቱ ይኖረዋል። በቀላሉ ተመልካቾቹ ወይም ታዳሚዎቹ ስለእርሱ እንዲያውቁ የሚፈፈልገውን ነገር እወቁልኝ ሳይል በብልሃት እንዲያውቁለት ወይም እንዲረዱት ማድረግ ትችላለህ።
2. ራስን መቆጣጠር /ራስን መግዛት/፡ ስሜትህን መቆጣጠር። ለሁኔታዎች በፍጥነት ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ስሜትህን አረጋግተህ እንዴት መመለስ /ምላሽ መስጠት/ እንዳለብህ ማሰብ ማለት ነው። ለሁኔታው አስፈላጊ የሆነውን በተገቢው መንገድ መመለስ። ራስህንም በተገቢው መንገድ መግለጽ ማለት እንደሆነ ጎልድማን ያስረዳል። በዚህ ወቅት ኢሞሽናል ማቹሪቲ ላይ የደረሰ ሰው የሚከተሉት መገለጫዎች ይኖሩታል።
- ሃላፊነትን መረዳት፡ በሚሰራቸው ሥራዎች እና በሚያከናውናቸው ውሳኔዎች ላይ ሙሉ ሃላፊነት ይወስዳል።
- ለለውጥ ራስን ያዘጋጃል፡ ወደፊት ለሚመጣ ማንኛውም ለውጥ ራሱን ምቹ አድርጎ ያዘጋጃል።
- አንድ ሰው ሲነጫነጭበት ወይም ነውረኛ ሲሆንበት በተመሳሳይ መንገድ ምላሽ አይሰጥም። እንደውም፣ በተቃራኒው ነገሮች እንዳይባባሱ በሚያስችል ስነስርዐት ምላሽ ይሰጣል። (በዚህ ደረጃ ላይ፣ ሰዎች ንዴታቸውን አንተ ላይ ሲያሳዩ ባንተ ብቻ እንዳልተናደዱ ተጨማሪ ምክኛቶች ሊኖራቸው ይችላል በማለት ለራሱ በመንገር ይረዳቸዋል፣ ይታገሳቸዋል። እንደውም መናደድ የሰዎች ባህሪይ መሆኑን በመረዳት ሰዎች ሲናደዱ እና ንዴታቸውንም የሚያንጸባርቁበት አንድ ሰው እንደሚያስፈልጋቸው ይረዳቸዋል።
3. የውስጥ ተነሳሽነት፡ የውስጥ ተነሳሽነትን ሲያብራራ ዳነኤል ጎልድማን እንዲህ ይላል። "የውስጥ ተነሳሽነት ብዙ ጊዜ ለመማር ወይም ለማወቅ በሚኖር ፍላጎት ይገለጻል። ራስን በገንዘብም በማህበራዊ ደረጃ ከፍ ለማድረግ በሚደረግ ፍላጎት ውስጥ ይገለጻል" ይለናል። ለምሳሌ አንድ ድሃ ሰው እየኖረው ያለውን የድህነት ህይወት መነሻ እና መፍትሄውን ለመረዳት ቢፈልግ የውስጥ ተነሳሽነት አለው ማለት ነው። ስለሆነም ስለሚኖርበት ማህበረሰብ፣ ስለቤተሰቡ አኗኗር፣ ስለሃገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ፣ የከተማዋ የሥራ አጥ ሁኔታ እና የተለያዩ ጉዳዮች ማሰላሰል ሲጀምር ከውስጥ ተነሳሽነት እንዳለው መናገር ይቻላል። ገነዘብ ወይም ሀብት እና ማህበራዊ ደረጃዎች (ማህበረሰቡ ለግለሰቡ የሚሰጠው ደረጃ አስተዋይ ሰው፣ አስታራቂ፣ የተከበረ፣ ነገረኛ፣ ሌባ፣ ...ወዘተ) በተለምዶ ውጫዊ አነሳሽ ጉዳዮች ናቸው። በዚህ ወቅት ኢሞሽናል ማቹሪቲ ላይ የደረሰ ሰው የሚከተሉት መገለጫዎች ይኖሩታል።
- ተልዕኮን ለማጠናቀቅ ፍቃደኝነት እና ቁርጠኝነት ያሳያል
- በጭንቅ እና በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ወቅት ጽናት የኖረዋል
4. የሌሎችን ስሜት መረዳት፡ "አንድ ሰው ይሄንን የኢሞሽናል ኢንተሊጀንስ መገለጫ ሊያሳካ የሚችለው ራሱን እና የራሱን ስሜት ማወቅና መረዳት ሲችል ብቻ ነው። ራሱን መረዳት የማይችል ሰው ሌሎችን ለመረዳት የሚያስችል አቅም የለውም!" በማለት ጎልድማን ባጭሩ ይገልጸዋል። ይህ ማለት፣ በጸብ መሃል ወንድሙን በሞት ያጠን አንድን ሰው ለመረዳት ስንፈለግ "ወንድሙን ገደሉበት ያሳዝናል" ብሎ ማሰብ ሳይሆን፣ "የሞተው የእኔ ወንድም ቢሆን በዚህ ሰአት ምን አይነት ስሜት ውስጥ ነው የምሆነው?" ብሎ ራስን መጠየቅ እና የሃዘንተኛውን ግለሰብ ትክክለኛ ስሜት ለመረዳት መሞከር ነው። በዚህ ወቅት ኢሞሽናል ማቹሪቲ ላይ የደረሰ ሰው የሚከተሉት መገለጫዎች ይኖሩታል።
- ሰውን መረዳት፡ የሌሎችን ስሜት ይረዳል፣ በጉዳዮቻቸውም ላይ ከልቡ ለመረዳት ፍላጎት ያሳያል። መፍትሄም ለመስጠት ይሞክራል።
- አጋዥነት፡ ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሳይጠይቁት ቀድሞ ይገምታል/ያውቃል ያቅሙንም ለመርዳት ይሞክራል
- የሰዎችን ስሜት በደንብ የተረዳን የቢሮ ፖለቲካ /Office Politics/ ወይም የሰዎች አሉባልታ ወይም ይሉኝታ ብዙም አያስጨንቀውም
5. ማህበራዊ ከህሎት፡ እንደ ዳነኤል ጎልድማን ማብራሪያ፣ "ማህበራዊ ግንኙነትን ለመገንባት እና የሁኔታዎችን ዝምድና በብቃት ለመቆጣጠር እና የጋራ ጉዳይ ለመፍጠር ማህበራዊ ክፍተቶችን ወይም አጋዥ ሁኔታዎችን መለየት" ማለት ነው። ይህ ግለሰብ በሚኖርበት ማህበረሰብ ውስጥ ምን ክፍተት አለ? ምን ባደርግ ይህንን ክፍተት መሙላት እችላለው? የምንላቸውን ጥያቄዎችን ራሱን በመጠየቅ ችግሩ ከማህበረሰቡ ጋር በጋራ እንዲፈታ ይሰራል። ለምሳሌ ስርቆት ወይም ሌላ ወንጀሎች በሚፈጸሙበት ወቅት ይህ ጉዳይ ውሎ አድሮ የእያንዳንዱን ነዋሪ ህይወት ሊጎዳ እንደሚችል ማህበረሰቡን በማስረዳት እና ጉዳዩን የማህበረሰቡ የጋራ ጉዳይ በማድረግ አስፈላጊውን ወንጀልን የመከላከል ሥራ እንዲሰራ ያደርጋል። በዚህ ወቅት ኢሞሽናል ማቹሪቲ ላይ የደረሰ ሰው የሚከተሉት መገለጫዎች ይኖሩታል።
- የተግባቦት /Communication Skills/ ችሎታ ይኖረዋል፡ በደንብ አዳምጦ በተገቢው መንገድ ምላሽ መስጠት ይችላል
- ተጽዕኖ ፈጣሪነት /Influential/ እና የአመራር /Leadership/ ከህሎት ይኖረዋል፡ ሌሎችን መምራትና ምሳሌ መሆን ይችላል
- ግጭት የመፍታት/Conflict Resolution/ ችሎታ ይኖረዋል፡ በማሳመን /Convincing/እና በመደራደር /Negotiation/ ከባድ አጋጣሚዎችን ማለፍ ይችላል።
ዋቢ ጽሁፎች
- http://inspirebusinesssolutions.com/blog/what-is-the-difference-between-emotional-intelligence-and-emotional-maturity
- http://inspirebusinesssolutions.com/blog/5-main-components-of-emotional-intelligence
- Peter Vajda, Ph.D. and True North Partnering፣ (2013)
- https://web.sonoma.edu/users/s/swijtink/teaching/philosophy_101/paper1/goleman.htm
- http://en.wikipedia.org/wiki/Emotional_intelligence
- http://www.unh.edu/emotional_intelligence/
- http://www.edge.org/q2005/q05_print.html#goleman
- http://www.eiconsortium.org/
- Answer, but No Cure, for a Social Disorder That Isolates Many
- Men, women and emotions - or why he never tells you how he’s feeling!